ጥናት 2 መልሶች

 የጥናት ሁለት መልሶች ከማብራሪያ ጋር 


ጳውሎስ እደነቃለው ሲል የተታለሉትን ገላትያውያን አማኞችን በዝግታ ሊመክር መጀመሩን አመላካች ነው። እደነቃለው ማለቱ ለእነርሱ ያለውን መልካም መገረም ለመግለጽ አይደለም። የጥሩ ክዋኔ ማበረታቻ ሳይሆን እንደውም እንዳፈረባቸው እና በተፈጠረው ሁኔታ ማዘኑን መቆጨቱን አመላካች ነው።

የጳውሎስ ዓላማ ለገላትያ አማኞች ፡ ወደ እውነተኛው የዳኑበት መንገድ እንዲመለሱ በመሆኑ በዝግታና በፍቅር ይናገራቸው ይጀምራል። ምክንያቱም ፡  በጳውሎስ እሳቤ ማንም ቢሳሳት ወደ መልካሙ መንገድ የሚቀናው ወይም የሚስተካከለው በፍቅር እንደሆነ ያምናል ያስተምራልም።

ሰዎችን ለመመለስ እየፈረዱ፤ እየጮሁ ፤እያጋጩ የመሄድን ዝንባሌ የጳውሎስ ንጹህ ወንጌል በትምህርቱ  አይደግፍም። ለተታለሉ ወገኖች ጥፋታቸውን ሳይሆን መመለሳቸውን መዳናቸውን ስለሚፈልግ በመልካም ንግግር በለዘበ አንደበት ንግግሩን “እደነቃለው “ በሚል የቁጭት እና የመሪር ሃዘን ቃል ይናገራቸዋል።

 እነዚህን የገላትያ አማኞች ነድፈው የበከሉዋቸው ተንኮለኞች መኖራቸውን መዘንጋት ውስጥ አልገባም ጳውሎስ በመልክቱ ። ነገር ግን  ጳውሎስ በወንጌሉ ስብከት ያመኑትን ወገኖች እንደ ወላጅ በ እንክብካቤ መገሰጽን መርጧል። ዋናው ትኩረቱ እነሱን ማትረፍ በመሆኑ ነው።

ጳውሎስ በፈተና ተሰናክለው ለወደቁ የሚራራ ቀና መንፈስን ተቀብሏል።  ስለ መንጋው እጅግ የሚገደው እረኛ ነበር። ቦታውንና ስሙን ለማስጠበቅ ሳይሆን ነፍሳትን ለማዳን ነበር ግቡ።   ነፍሳትን ለማዳን ነበር በብዙ ሺ የሚቆጠር ኪሎሜትሮችን በብዙ ስቃይ እና መከራ ተጉዞ ወንጌሉን በሚሲዮነነት ሲያዳርስ የነበረው።

ለህይወቱ ሳይሳሳ የኖረለት ወንጌል ነፍሳት እንዲድኑ ነውና እንዲሁ በቀላሉ ልቡ የአማኞችን መጥፋት መመልከት አይችልም። በ መከራቸው እሳት ላይ ፡  የማማባሻ ፍርድን መጨመር አልነበረም ግቡ  ይልቅስ እነርሱን ከገቡበት ቅርቃር አውጥቶ ማራመድ ነበር።

ዛሬ ዛሬ ስለ ዝናቸው እና ስማቸው እንዲሁም ስላሉበት ቦታ እንጂ ስለ አማኙ ህይወት የማይገዳቸው ቤተ ክርስቲያንን የተቆጣጠሩ ፓለቲከኞች፤ግድ የለሽ ዓለማውያን ፤ ያልተሰጡ አገልጋዮች የነፍሳት መጥፋትን እንደቀልድ ሲያወሩ ይደመጣል።

እነዚህ አመራር ላይ ያሉ በየቤተ እመነቱ የተሰገሰጉ ሙያተኞች ፤ የተረበሹ ህሊናዎችን ከማረጋገት እና ከመመለስ ይልቅ በጎቹን እንዲደነብሩ በማድረግ ለ አውሬ አውጥተው የሚጥሉ ሆነዋል።  በቁስላቸውም እንጨት የሚሰዱ ፤ የስብራታቸው ቀዳዳን የሚተረትሩ ጨካኞች በዝተዋል። ጳውሎስ ዛሬም ለ እንደዚህ አይነቶቹ ጨካኞች መልዕክት አለው።

ልዩ ወንጌል ፡ ሃሳዊ አስተምሮዎች ፈጽሞ ስህተታቸውን ፤ ሌብነታቸውን፤ ነፍሰ ገዳይነታውቸውን አያስተዋውቁም።  ዲያብሎስ ሁሌም የጦር እቃዎቹንና ድርጊቶቹን ይሸፋፍናል። እርሱ በሚስጥር እና በምሽግ የሚዋጋ ቢሆንም የብርሃን መላአክ እስኪመስል ድረስ እራሱን ይቀያይራል።  በሚያስገርም ሁኔታ ዲያብሎስ የግል ንብረቱ የሆነውን መርዛማነት በ ክርስቶስ ወንጌል ውስጥ ለመጨመር ብርቱ ነው።

ጳውሎስ የሰይጣንን ተንኮል ስላወቀ ለገላትያ ሰዎች ሌላ ወንጌል ወይንም እንግዳ ወንጌል ይዛችሁል ይላል።  እኔ ያበሰርኳችሁ ወንጌል በእናንተ አልታመነም አልቆየም  ። ውሸታሞቹ ሃዋርያት ነን ባዮች የ ጳውሎስ ወንጌል ሙሉ እንዳልሆነ እና ለመዳን በክርስቶስ ማመን ብቻውን በቂ አለመሆኑን ነበር ለገላትያ ሰዎች የሚያስተምሩት።

 ዲያብሎስ ወንጌሉን ሊያጠፋ እንዳልቻለ ሲያይ እንደ አማራጭ የወሰደው መንገድ ፤ ወንጌሉ ይሻሻል ወይም ይስተካከል በሚል ሰበብ እንክርዳዱን መዝራት ነው። ይህ ማለት የሰው ስራ ይጨመርበት በሚል እሳቤ ወንጌሉን  ማጣመም ጀመረ እንደማለት ነው ።

ዲያብሎስ አማንያን በማጠር ፤በመከራና በስቃይ አሳልፎ ቢሰጣቸውም ፤ በጊዜው የገጠማቸውን መከራና ሰቆቃን እንደ ሙሉ ደስታ በመቁጠር ድል ስለነሱት ፤ ቀጣይ አማራጩ ወንጌሉን በሚጠቅም አስመሳይነት  መበረዝን እንደ አማርጭ  አድርጎ ወጣ። ከመካከላቸውም ጥመትን በመዝራት እነ ጳውሎስ አስቀድመው ካስተማሩት ወንጌል ጭማሪ ሚስጥራዊ እውቀት እንደተገለጠ  ይህም ደግሞ ክርስትያኖች እንዲያስቡበት በማድረግ ማሳት ጀመረ።

ይህ መበረዝ እና መቀየጥ ነው ወንጌል ላይ ከፍተኛ ችግር የሚፈጥረው። መጋደላችህን ጦርነታችን ከስጋ እና ደም ጋር አይደለም ። ጦርነታችን ከ ማይታዩ ከ  ጨለማ ሃይላት፤ ስልጣናት ግዢዎች እና ከዚህ ዓለም መንፈሳዊ ክፋት ጋር ነው። እንደተባለው የክፋቱ ሁሉ ምንጭ ዲያብሎስ ነበረ።

በክርስቶስ ጸጋ እናንተን ከጠራችሁ ከእርሱ ፡ ይህ የምንኖርበት ምድር በሰይጣን የታሰረ በመሆኑ የዚህች ምድር ነዋሪዎች ወንጌሉን ለመቀበል እና ለማስተናገድ ጣር ውስጥ ሲገቡ እናስተውላለን። በወንጌሉ ከመደሰት ይልቅ ፤ በምድር ጭለማ መዝናናትን ይመርጣሉ።

ወንጌል ለሰው ልጆች እጅግ ጠቃሚ ነገሮችን ለአብነትም ያህል የዘላለም ህይወት ፤ እረፍትየህሊና ሰላም  ይዞ የመጣ ብዙ ኪሳራን ያስቀረ መልካም ጉዳይ ቢሆንም ፤ ወንጌሉ በዚህ ምድር የገጠመው መሰደድ እና መከራ ነበር። ለዚህ ጠቃሚ ወንጌል የምድር ምላሽ በጎ አልነበረም። ለጻድቁ እየሱስ መስቀል እቺ ምድር የነበራት መስቀል ነበር። እንዲሁ ለጸጋው ወንጌል ቦታ ያጣች ምድር ናት።

እነዚህ አስተማሪዎች በክርስቶስ የሆነው ጸጋ አስክደው የገላትያ ሰዎችን ወደ ህግ እንዲዛወሩ ጨቋኝ የሆነ የባርነት ትምህርትን ያስተምሯቸው ጀመሩ። እናም ጳውሎስ በደብዳቤው  እንዴት ከዚህ ህይወት፤ ሰላም ፤ ነጻነት እና በረከት ከሞላበት ትታችሁ ወደ እስራት እና ባርነት በፍጥነት ለመዛውር ከጀላችሁ ወይም ሆነላችሁ??  እያላቸው ነው። በአግራሞት ዘይቤ እየተናገረ ያለው  እንዴት ራሳችሁን ለዚህ ባርነት ለመስጠት በቀላሉ ትሸነፋላችሁን? እያላቸው ነው።

ፈጥናቹ ሲል ጳውሎስ የገላትያ ቤተ ክርስትያናትን ጳውሎስ በብዙ መከራና ጥረት የተገነባች ብትሆንም ገና እግሩ ገላትያ ምድርን ከመልቀቁ የሃሰት መምህራን እና ሰባኪዎች አማኞቹን ወደ ውዥንብር በመክተት የቆሙበትን እውነት እንዲጠራጠሩ እና ወደ እንግዳ ሃሳብ ዘወር እንዲሉ አድርገዋቸዋል። ይህም እጅግ አጭር በሚባል ጊዜ ውስጥ መገልበጣቸውን አመላካች ነው።

 በ እውነተኛ ወንጌል በብዙ የተሰዉ ጊዜያት እና አመታት የተገነቡ እውነቶች በክፋት እርሾ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ተበርዞ ማየቱ ጳውሎስን አስደንቆታል። እነዚህ አሳሳቾች በፍጥነት የሚሰሩበት ዋና ምክንያት፡ እጅግ ደፋር በመሆናቸው ነው ። ምክንያቱም ደግሞ በምንም መከራ እና ችግር ስላለፉ ምንም ጥረት ያላደረጉበትን ነገር ሊጠነቀቁለት አይችሉም።

 በጣም በመልከት ያለብን ነገር ዲያብሎስ እንዴት በስንዴው መሃል ፤  ተኝተን ሳለን  እንክርዳዱን እንደሚዘራ ነው።  ጳውሎስ ፊቱን ከገላትያ መልሶ ወደ ሌላ ሃገራት ሰበካ በዞረበት ቅጽበት ሃሰተኞቹ መመህራን ገላትያን አጥለቀለቋት።

ዛሬም እንዲሁ ነው ሃሰተኞችን ቀዳዳ እያገኙ እውነተኛዋን ቤተ ክርስትያን እንዳይበርዟት እጅግ ጥንቃቄ ይሻል። እረኞች ሁሌም መንጋውን ለመጠበቅ ንቁዎች መሆን እንዳለባቸው ያሳየናል። ዲያብሎስ ክፍተቱን ተጠቅሞ ፍሬ የሌለውን የትዕቢት ዘር በንጹህ እርሻው ውስጥ ለመዝራት የሚያደባ አጥፊ በመሆኑ ለመሰብሰባችን መጠንቀቅ እንዳለብን ያስተምረናል።

እንዳለፋቹ : ሓዋርያው ጳውሎስ የገላትያ አብያተክርስትያናትን  እናንተ ክፉዎች እና ከሃዲዎች አልነበረም ያላቸው። ይልቅስ ብዙ አጥተው እየተሰቃዩ ያሉ እና በመከራ ውስጥ እንግዳ ነገር እንደገጠማቸው አድርጎ ይናገራል። ቅድም እንዳልነው የጳውሎስ ዓላማ ቤተክርስትያኒቱን መታደግ እንጂ በፍርድ ማውደቅ አልነበረም።

ወደዚህ ደግሞ መከራ እንዲገቡ ያረጋቸውን ይገስጻል። የደብዳቤው ጦር በውጤቶቹ ላይ ሳይሆን በመንሴው ላይ ነበር ያደረገው።  ይህ የሚያሳየን ስር የሰደደ እምነት በቃሉ ላይ እንዳልነበራቸው ነው።  የገለትያ አብያተክርስትያናት  በቀላሉ ያያዙትን ነገር ትተው ለመሄድ ቀሏቸዋል። ከጠንካራው ወጥነታቸው በቀላሉ ገሸሽ ማለታቸው አስገራሚ እና የሚያበሳጭ ድርጊት ነበር ለጳውሎስ ። 

ቃሉን ሲቀበሉ እጅግ ደስተኞች ፤ ቅናት ውስጣቸው የሞላ ፤ ለማገልገል ትልቅ ሸክም ያላቸው ነበሩ።  በጊዜ ማዕበል ውስጥ ግን  ደክመው ቃሉን ለማየት እንኳ ዝለው ልናገኛቸው ችለናል። የገላትያ ሰዎች ገጠመኝ ለሁላችንም አስተማሪ መልክት አለው።

እርሱ ግን ሌላ ወንጌል አይደለም:  ጳውሎስ እነዚህን አሳቾች እያወገዘ ነው።  እነርሱ እርሱን ሃሰተኛ ወይም ጎዶሎ ወንጌል ይሰብካል እያሉ ችግር ቢፈጥሩበትም እርሱ ደሞ ምላሽ እየሰጣቸው ነው። ጳውሎስ ያስቀረባችሁ ነገር አለ ለሚሉት ሃዋርያት ነን ባዮች ውሸት ነው ምንም አዲስ ነገር የላቸውም እኔ የነገርኳችሁ የተቀበልኩትን ሙሉውን ነው እያለ ነው።

የሚያናውጡአችሁ የክርስቶስንም ወንጌል ሊያጣምሙ የሚወዱ አንዳንዶች አሉ እንጂ ይላል ምክንያቱም እነዚህ ሃሰተኛ ሃዋርያት ህዝቡን መገረዝ አለባችሁ እያሉ ያስተምሩ ነበር። ጳውሎስን ከ ሙሴ ህግ ያፈነገጠ አስተምሮ እንዳለው በመናገር የ እግዚአብሄርን እና የ አይሁድን ህግ እንደሻረ ይናገሩ ነበር።

ስለዚህ ጳውሎስ ገላትያ ሰዎችን በፍቅር ይዞ እነዚህን ግን ሃሰተኞች ማውገዝ ይጀምራል። እነዚህ አይሁድ ነን ባይ ሃሰተኞች የገላትያ አማኞችን እጅግ ያስቸግሯቸው  ወይም ችግር ፈጥረውባቸው ነበር ።  ነገር ግን ይህ ብቻ አልነበረም ከዚህ አልፎ የ ክርስቶስን ወንጌል ያጠፉ ነበር። እነዚህ የሃሰት ሃዋርያት ወንጌሉንና  ህግን ያዛቡ ነበር። ጸጋ እና ህግ ያላቸውን ግንኙነት በማዘበራረቅ ግርታን ፈጥረዋል።

ክርስቶስ እና ህግ በህሊናችን በጋራ መኖር አይችሉም አንዱን መምረጥ አለብን ብለው ያስተምሩ ነበር። አላማቸውም የክርስቶስን ወንጌል መደምሰስ ነበር። ህግ እና ወንጌልን መቀላቀል ወይም አንድ ማድረግ ቀላል ሊመስለን ይችላል ። ነገር ግን ከክርስቶስ ጋር ያለንን ግንኙነት የሚያዛባ ሂደት ነው ውጤቱ የሚሆነው።

ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን።  ጳውሎስ በመጀመሪያ ራሱን ለመርገም ደፍሯል ምክንያቱም የሰበከው ወንጌል እርሱ የፈጠረው ባለመሆኑ ነው። ወንጌሉን ሙሉ በሙሉ ሳይሰሰት ሳያሰቀር የተላከውን አድርሷል። ከተናገረው ወንጌል ሻል ያለ ወንጌል የለውም ወደፌትም አያመጣም ለ አንዴና ለመጨረሻ የመይለወጠው እግዚአብሄር አብ ልጁም እየሱስ ክርስቶስ ሰጥተውት ነው የሰበከው። ለዚህም እጥፍ ብል የተረገምኩ ልሁን እያለ ነው።

ጳውሎስ እግዚአብሄር በቅዱሳን መጽሃፍ ያስቀመጠው እውነት ነበር የተናገረው። ስለዚህ የመጀመሪያዎቹ የስህተት ምንጮች ሰዎች በመሆናቸው ሰዎችን ጨምሮ መላክት ቢሆኑ እንኳ ከተሰበከው ወንጌል እውነት ውጪ ቢሰብኩ የተረገሙ ይሁኑ ይላል። ይህም ወንጌሉ ወደፊት ባህልን፤ የተፈጥሮ አቀማመጥን፤ ቴክኖሎጂን ተገን አድርጎ የሚሻሻል እውቀት አለመሆኑን አስረግጦ ይናገራል።

አስቀድመን እንዳልን እንዲሁ አሁን ሁለተኛ እላለሁ፥ ከተቀበላችሁት የተለየውን ማንም ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን። ጳውሎስ ደግሞ ይናገራል በውስጡ ታላቅ ቁጭት ስላለ ማንም እርሱ ከሰበከው ወንጌል ውጪ የተሻሻል ወንጌል ማቅረብ እንደማይችል ይገልጻል። ማናችንም ብንሆን ምስክሮች እንጂ አራሚዎች ወይም ሊቃውንት አይደለንም ። ከ እየሱስ ክርስቶስ እና ከመጽሃፍት በላይ መሆን አንችልም። እግዚአብሄር በእየሱስ ከገለጠው ወንጌል የተሻሻለ ወንጌል ሊኖረን ፈጽሞ አይችልም እያለ እያስረዳ ነው። ይህንንም አስረግጦ ይናገራል ከዚህም ወንጌል ያፈነገጠ የሚሰብክ የተረገመ ይሁን ይላል።

ውን ወይስ እግዚአብሔርን አሁን እሺ አሰኛለሁን?

 እናንተ የገላትያ ሰዎች እስኪ ንገሩኝ እያለ እየጠየቀ ነው።  ይህንን ማወቅ አለባችሁ ፤ ብብዙ መከራና ስቃይ አልፌ ወንጌሉን አንዳድረስኩላችሁ ተመልከቱ እያለ ነው። በዚህም ሰውን ወይስ እግዚአብሄርን እንዳገለግለኩ እናንተው ፍረዱ እያለ ነው።

በ አስተምሮው ከሰው ዝናን እና ከበሬታን ወይም ተቀባይነትን ለመግኘት አይደለም የለፋው።  ያስተማርነው እውነት ሰዎች በራሳቸው አንዳች ማድረግ የማይችሉ መሆናቸውን ነበር።  እንዲሁም የሰው ነጻ ፈቃድ ፣ ብቃት እና ጽድቅን ሰላምን እንደማይሰጡ አውግዘን አስተምረናል። ለዛም የ እግዚአብሄርን ጽድቅ ፍጹም በክርስቶስ እርዳታ የምናገኘው መሆኑን አስረድተናል። እያለ ነው።

 ይህ ሰበካችንም ሰዎችን ለማስደሰት አልነበረም። ሰዎችን ደስ ላማሰኘት ጥረን ቢሆንማ ኖሮ በዚህ ዓለም መከራ ፤ መገረፍ፤ መገደል እና ማስፈራራት ባልደረሰብን።  የ እግዚአብሄር ደስታ የሆነውም እንጂ ለሰው ደስታ አላገለገልንም።  

ያስተማርኩት ከሰማይ የታዘዝኩትን እንጂ ለስጋ እና ደም ለምድር አመለካከት ያዋጣል የተባለውን ሁኔታ አልሰበኩም ። ያስተምርኩት ወንጌል ፈጽሞ መለኮታዊ ነው ። ከ አንዱ መለኮታዊ ትምህርት ውጪ ያለው ሁሉ ሰይጣናዊ ስጋዊ እና ለሰው ደስታ የተፈበረከ ነው።

ከዚህም የተለየ ወንጌል የተረገመ እና ውሸት ነው። በ አስመሳይነት የተሸረበ ለሰው ችሎታ አድናቆትና ክብርን የሚለግስ ሃሳዊ ትምህርት ነው። እኛ የምንሰብከው እውነተኛውን ከ እግዚአብሄር ብቻ የሆነውን ወንጌል ነው።  ይህም በክርስቶስ የጽድቅና የሞገስ አዳዳን ብቻ የሚታመን እውነተኛ ትምህርት ነው። ከዚህ ውጪ ያለው በጠቅላላ በሰይጣን የተላኩ መምህራን ያመጡት ፎርጂድ ወንጌል ነው። እያለ እያስረዳ ነው።

ሓሰተኞች ብዙዎች ሰዎችን በማስደሰት በሰላምና በ እረፍት ለመኖር ይሞክራሉ። ለሰው ልጆች ህሊና ተስማሚ የሆነ ነገር ከ እግዚአብሄር ሃሳብ ጋር ተቃረነ ተስማማ ግድ ሳይሰጣቸው ከማህረሰቡ ጋር ተስማሚነት ያለውን አስተምሮ ያቀርባሉ ።

እኛ ግን ስለ አስተምሮዓችን የሚመጣውን ተቃውሞ ሁሉ ችለን ወንጌሉን ስንሰብክ ነበር። እያለ ነበር ጳውሎስ።

አሁን ሰውን ደስ ባሰኝ የክርስቶስ ባሪያ ባልሆንሁም ጳውሎስ አንዳንዶችን ለላመሰናከል ሲል አንዳንድ የ አይሁድ ህግጋትና ስራአትን መጠበቁ ጳውሎስ በአይሁድ ወንድሞቹ መካከል ተሸናፊ እንደሆነ የቆጠሩ ሃሳዊ ሃዋርያት ነበሩ።

ጳውሎስ ጤሞቲውስን እንደገረዘው በ ኢየሩሳሌም የመንጻት ስራአትን ከ አራት ሰዎች ጋር ማድረጉን የወንጌሉ ድክመት ማሳያ አርገው በማቅረብ ይከራከሩት ነበር። ጳውሎስ ሁሉን ያደረገው ሰዎችን ከመሰናከል ለመጠበቅ ቢሆንም እነርሱ እንደ ድካም ወስደውበታል።  

ጳውሎስ ግን አይሁድን ስራዓት ለወንጌሉ ዋና አድርጎ ወስዶ ቢሆን ይህ ሁሉ አለምስማማት ባልተፈጠረ፤  እነርሱም ባመሰገኑት ነበር። እውነታው ግን እርሱ ፈጽሞ የክርስቶስ ጽድቅ ያለምንም የሰው ፍቃድና ጥበብ ወይም ሃይል  በ እምነት በጸጋ ብቻ የሆነ ድነት መሆኑን ማስተማሩ ነበር ተቃውሞን ያስነሳበት።

ተባረኩ!  


Comments

Post a Comment

የአንባቢዎች ብዛት

Popular posts from this blog

የገላትያ መጽሐፍ ጥናት 1

ጥናት 2 ጥያቄዎች