ትውውቅ መግቢያ (1:1-5)-ማብራሪያ
መልሶች
ሓዋርያነቱ ፡
o በኢየሱስ ክርስቶስ የሆነ
o በ እግዚአብሄር አብ የሆነ
o ከሰዎች ያልሆነ
o በሰዎች ያልሆነ
ጳውሎስ ገላትያ ክልልን ለቅቆ ከሄደ በኋላ ፈናቲክ(ኤክስትሪሚስት) “ጭፍን” አመለካከት ያላቸው አይሁዳውያን በቤት እምነቶቹ መግባታቸው በክርስቶስ እየሱስ የሚገኘውን ነጻ የጽድቅ ትምህርት በማጣመም በሃይማኖታዊ ጥበብ እና ስራዓቶች በመቀየጥ ንጹሁን ወንጌል መበረዛቸው ነበር መልዕክቱን ለመጻፍ ያነሳሳው።
ወንጌሉ በአነሳሱ ሃይማኖታዊ ስራዓቶችን እየደገፈ እያበረታታ የመጣ ሳይሆን ፈንቅሎ የወጣ እንግዳ ነገር ነው። በሃይማኖታዊና ማህበራዊ ስራዓቶች የነበረውን ተቀባይነት ያለው ድርጊት፤ ባህል እና ስምምነት የናደ ታላቅ አብዮት ነው። ወንጌሉ በዚህ ዓለም ክስ ቀርቦበታል። ወንጌሉን በ እግዚአብሄርና በሰው ላይ የተነሳ ምድርን የወረረ እጅግ ክፉ ወረርሽን ነው ትል ነበር አለም።
በሌላ መልኩ ወንጌሉ ለዓለም በክርስቶስ እየሱስ የሚሆንን ድነት ፤ የህሊና ሰላምን እና በረከትን አምጥቷል። ዓለም የጠላችው በዚህ ምክንያት ነው።
እነዚህ ወግ አጥባቂ ጭፍን አይሁዳውያን
- · ትክክለኛ የአብርሃም ነገድ መሆናቸውን
- · እውነተኛ የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ መሆናቸውን
- · በእውነተኞቹ ሃዋርያት የተማሩ መሆናቸው
- · ተዓምራትን ማድረግ እንድሚችሉ
· እነዚህ ሃሰተኞች የጳውሎስን ሃዋርያዊ ስልጣን ያጣጥሉ ነበር፤ ጳውሎስ የመጨረሻ እንደሆነ ከነሱ በታች እንደሆነ፤ ክርስቶስን እነሱ እንዳዩት እና በአካል እንድሚያውቁት ፤ ሲያስተምር ከአፉ እንደሰሙ ፤ መንፈስ ቅዱስን እንደተቀበሉ እና እንደማይሳሳቱ ፤ ጳውሎስ ቤተክርስቲያንን አሳዳጅ እንደነበረ ለረጅም ጊዜ ፤ እየሱስን እንዳላየው ፤ ከአይሁዳዊ ሃዋርያትም ጋር መልካም ግንኙነት እንደሌለው በገላትያ ክልል ላሉ አማኞች ይናገሩ ነበር።
እነዚህ ሰዎች ያሉበትን እና የነበራቸውን ደረጃ በማውሳት ተቀባይነት ለማግኘት ጥረት ያደርጉ ነበር። በተመሳሳይ በዚህ ዘመንም ሃይማኖታዊ ብቁነትን እና ትክክለኛነትን በቀዳሚነት የሚለኩ አይጠፉም። ጳውሎስ መጤ ወንጌል ነው ያለው ተብሎ ክስ እንደ ቀረበበት ፤ ዛሬም የተጣበቁበትን ምድራዊ የሰው የስራዓት ፍቅር ለመላቀቅ የሚቸግራቸው ብዙዎች ናቸው። በ እነዚህ አስተማሪዎች የተነሳ የጳውሎስ አስተምሮ በገላትያ በሚገኙ አማኞች ጥያቄ ውስጥ ገብቶ ነበር።
ጳውሎስ በ እነዚህ ሃሰተኛ መምህራን ፤ ሓዋርያት ተሰብሮ ኋላ አልቀረም። እንደውም እነሱ ዋና የሚሉትን ሓዋርያው ጴጥሮስን ሳይቀር ፊት ለፊት እንደተቃወመው በገላትያ በላከው ደብዳቤ ያወራል። ለዚህም ነው ጳውሎስ ሃዋርያዊ ስልጣኑን በሰው የተሾመለት እንዳልሆነ የሚገልጽው። ሰው አላላከኝም እያለ ነው። ሃዋርያት ሃዋርያ አላረጉኝም እያለ ነው። ሃዋርያት ጸልየው ማቲያስ እጣ ወጥቶትለት ይሁዳን ተካ ጳውሎስ ግን ለሃዋርያነቱ ሿሚው በሰው ፊት የሆነለት ነገር አልነበረም። ሃዋርያዊ ሹመቱ በ እየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ይህም ከ እግዚአብሄር አምላክ እንደሆነ ይገልጻል። እነሱ ጴጥሮስ ላከኝ ቢሉ እኔ እየሱስ ራሱ ላከኝ ነው የምለው የሚል ይመስላል። አስከፊው ነገር ደግሞ ሃሰተኞቹ ጴጥሮስ ወይም ሌሎች ሃዋርያት ሳይሆኑ እራሳቸውን በራሳቸው የላኩ መሆኑም ነበር።
ዛሬም ዋና በጥባጭ በታዋቂ እከሌ ስም ራሱን በራሱ የሾመ ጭፍን ነው። ስለዚህም ራሳቸውን የሾሙ ወይም እግዚአብሄር በሰው በኩል የሾማቸው ቢሆኑ እንኳ እርሱ ሁለቱንም አለመሆኑን ይልቅስ እራሱ እግዚአብሄር ያለማንም ወኪል እንደሾመው ይናገራል። ስለዚህ እንደማትያስም ወንደ እነርሱም ሳይሆን እንደቀደሙት ሃዋርያት በቀጥታ በ እየሱስ ክርስቶስ ተሹሜያለው እያለ ነው።
ሌላው ወንጌሉን የተቀበለው ከሰው አልነበረም። እከሌ ሃዋርያ አሰልጥኖት ወይም አስተምሮት የሚያስተምረው ወንጌል አይደለም። ጳውሎስ ወንጌሉን ከ እየሱስ ክርስቶስ እንደተቀበለ ይህም በ እግዚአብሄር አምላክ እንደተላከለት ይናገራል። ለዚህም እርሱስ ከሰበከው ወንጌል ውጪ መላዕክት እንኳ የመስበክ ትክክለኝነት እና እውነትነት እንደሌለው ያትታል። ብሎም የሚሰብክ ቢኖር የተረገመ እንደሚሆን ቁጭቱን እና ምሬቱን ይናገራል።
ሁሉም መምህራን ፤ሃዋርያት ወይም ከ እግዚአብሄር ተልከው የመጡ ሰዎች በትክክል ከ እግዚአብሄር ለአግልግሎት መጠራታቸውን ብሎም ደግሞ ለሚያድርሱት ህዝብ የመናገር ተቀባይነት ለማግኘት ትልቅ ጥረት ማድረግ ይጠብቅባቸዋል። ይህ ማለት ለምሳሌ አንድ ሚሲዮናዊ አምባሳደር ሃገሩን ወክሎ በሌላ ሃገር በሚሰራው ስራ ተቀባይነት እንዲያገኝ ደጋግሞ ደጋግሞ የተላከበትን ሃገር በማውሳት ሲናገር ይደመጣል። ተቀባይነት ለማግኘት ሃዋርያት ሃዋርያነታቸውን ማጉላት ይገባቸዋል ! ይህ ምናልባትም የተሰጣቸውን ስጦታ በማጣጣል ተቀባይነት ለማግኘት ለሚሞክሩ ምስኪኖች መልስ ነው። ሓዋርያ ጳውሎስም ራሱን ሲያጣጥል አንመለከትም ይልቅስ ሃዋርያዊ ስልጣኑን አጉልቶ ሲያሳይ እንመለከታለን። ነገር ግን ጳውሎስ ትኩረቱ እግዚአብሄርን ልጁንም እየሱ ክርስቶስን ማክበር ነው።
የላከውን ስለሚያውቅ አገልግሎቱን እና ሃዋርያዊ ሹመቱን አክብሮ ያሳያል። እንደ ተርሴሱ ሳውል ሳይሆን እንደ ሃዋርያው ጳውሎስ አድምጡኝ ይላል። ለ እግልግሎት መሾም የ እወቅት ውይንም የችሎታዎች ጉዳይ ሳይሆን ለአግልግሎቱ የመመረጥ ጉዳይ ነው።
ለዚህም አገልግሎታችን ሊያስጨንቀን የሚገባን በሰዎች ዘንድ ለመከበር፤ ለገንዘብ ፤ ለደስታቸው ሳይሆን እርግጠኛ መሆን ያለብን በ እግዚአብሄር እንደተላክንና የምንስተላልፈው መልክት የግዚአብሄር ሃሳብ መሆኑና ከርሱ እንደተቀበልነው ነው።
ጳውሎስ እግዚአብሄር አብን ሲገልጽ ከ እየሱስ ትንሳኤ ጋር አያይዞ ነው የሚገልጸው። ይህም የወንጌሉን ይዘት መንደርደሪያ የሚያሳይ ነው። የየሱስ ትንሳኤ በመልክቶቹ ሁሉ የሚደጋግመው ጉዳይ ነው። የ እየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ በህግ ላይ ድል እንደነሳ ፤ በሃጥያት ላይ ፤ስጋ ላይ ፤ዓለም ላይ ፤ ሞት ላይ ፤ ሲኦል ላይ እና በማንኛውም ክፋት ላይ ሁሉ ድል ነስቷል ። ስለዚህም የሚታዩና የማይታዩ ሃይላት፤ ገዚዎችና ስልጣናት እግዚአብሄር በልጁ የለገሰንን ድልነሺነት ጠምዝዘው ሊውስዱ ቢያስፈራሩንም ሊነጥቁን እንደማይችሉ የእየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ የድላችን ማረጋገጫ ነው። ለዚህም ነው የሁሌም የጳውሎስ የትኩረት ማዕከል ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
ጳውሎስ ከእኔ ጋር ያሉትን ወንድሞች ማለቱ በ አግልግሎቱ እና በያዘው እውነት ብቻውን አለመሆኑን ያሳያል። ወንድሞች አብረውት እንዳሉ ይገልጻል። አብረውኝ ያሉት ምንም እንኳ ሃዋርያት ባይሆንም ከማስተምረው ትምህርት ጋር የትስማሙ ወንድሞች ናቸው እያለ ነው።
በገላትያ አብያተክርስትያናት ማለት በገላትያ የሚገኙ ቤተ ክርስትያኖችን እንደማለት ነው። ገላትያ አንዲት ቤተክርስትያን ብትሆንም በገላትያ ግን ያሉ ቤተክርስትያኖች ስብስብ ናት። የሃሰተኞች ዋነኛ ባህሪ ምንም ባልተዘራበት ሄዶ ዘርቶ ማጨድ ሳይሆን የበቀለበትን ቦታ ሄዶ መዝረፍ ነው። ሃሰተኞቹ ጳውሎስ ሆነ ሌሎች ሰዎች ያልሰበኩበት ቦታ አልሄዱም በዛ ደህነነት አልተሳማቸውም ሰዎች ሊያጠቋቸው ይችላሉ። ይልቅስ ምስኪኖች አይቃውሙንም ብለው ያሰቧቸውን የተሰበኩትን ክርስቶያኖችን አጠቁ ። ለ እግዚአሄር አገልጋዮች ትልቁ ህመም በዓለም የሚደርስባቸው ተቃውሞ እና እንግልት ይልቅ በተንከባከቡት ህዝብ ላይ የሚደርስ የወንጌል መቀየጥ እንዲሁም ሞኞች ናቸው ብለው በጭፍን ትምህርታቸው በሚንቀሳቀሱ የሃሰት መምህራን እና ሃሳዊ ልምምድ በሚያሳዩ አገልጋዮች ነው።
ገላትያ ቤተ ክርስትያን አልነበረም ለምን ቤተ ክርስቲያን ተባሉ? በተጨማሪ የክርስቶስን ወንጌል ትተዋል በእንግዳ ትምህርት ተበርዘዋል እንዴት ቤተ ክርስቲያን ይባላሉ? ለሚሉ ምናልባት በገላትያ ክልል በ እውነት ጸንተው የቆዩ ቅሬታውች ይኖራሉ። የ ክርስቶስ ተቃዋሚ የሰይጣን ዙፋን ያለባት እንኳ ቤተክርስቲያን ተብላ ነበር ። ስለዚህ ቤተ ክርስትያን ለማለት ወንጌል የሰማች የተቀበለች ብትደክም እንኳ በውስጧ ስላሉ ውድ ስጦታዎች የ እግዚአብሄር ልጆች ሲባል ቤተ ክርስቲያንንቷ የተጠበቀ ነው። የቤተ ክርስቲያን ዋስትና የክርስቶስ ጸጋ እና ጽድቅ መኖሩ ነው።
ጸጋ እና ሰላም ሁሌም ጳውሎስ የሚናገራቸው ነገሮች ናቸው። ጸጋ እና ሰላም በሰው ልጆች ደካማነት ለመቀበል ስለማይፈቅዷቸው ሁሌም በጆሮዓችን እየተደጋገመ መነገር ያለባቸው ታላቅ ስጦታዎች ናቸው። ጸጋ የሓጥያትን እዳ ሲከፍል ሰላም የህሊናን ጩኽት ጸጥ ያሰኛል። ኃጥያት እና የህሊና ክስ ገርፈውናል እየሱስ ክርስቶስ ደግሞ እነዚህን ዲያብሎሶቻችንን ለዛሬ እና ለዘላለም አስወግዷቸዋል። ይህንን የድል ነሺነት እውቀት ከሰማይ ያላቸው ክርስቲያኖች ብቻ ናቸው። ለሰዎች እጅግ ከባዱ እንዲሁ በጸጋ እና ብሰላሙ ተሞልታችኋል ብሎ ማሳመን ነው። ያለ ህግ ያለ ጥረት በሰማይ በሆነ ስጦታ ድል ነሺ ናቹ ስንላቸው ሰዎች ላያምኑን ይችላሉ። ባያምኑንም ቡሉ ተቃውሞ እና ሙግት ቢገጥመንም ጸጋ እና ሰላምን ከ እግዚአብሄር ተቀብለናል። ብዙ ተሞክሯል ብዙ ህግ ሲወጣ ብዙ ጥርጣሬ እና ግድፈት በዝቷል። በሰጠን ጸጋ ላይ እስካልተጣበቅን ድረስ ለተፈርፈሪው አጥንታችን እርፈት እሚሆነን ነገር የለንም።
ይህ ሰላም ከ እከሌ ይሁን አላለም ። ሰላሙ ምድር ላይ ያለ አይነት ሰላም አይደለም። ሰማያዊ ሰላም ነው። ፓለቲካው ፤ ማህበራዊ ሁኔታው ወይም ኤኮኖሚው ስለሚያመጣው ሰላም አይደለም የሚያወራው ይልቅስ ከ ላይ ከ እግዚአብሄር ስለሚቸር የህሊና ሰላም ነው። ይህ የውስጥ ሰላም ውጫዊ ስጋትና ችግሮችን ሞትን እንኳ ቢሆን ተጋፍጦ እንዲያሸንፍ ለ አማኝ ብርታቱ ነው።
ጳውሎስ ከ እግዚአብሄር ከአባታችን ካለ ብኋላ ለምን ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ አለ? በመጽሃፍ ቅዱስ አንድ ወሳኝ መመሪያ አለ። እግዚአብሄር አምላክ አይታይም ያየውም ደሞ በህይወት መኖር አይችልም። የ አምላክነት ምስጢሩን እጅግ ለመረዳት መሞከር አክሳሪ ነው። መጽሃፍ ቅዱስ እግዚአብሄርን አምላክነት በማስረዳት አይደለም ትኩረቱ ይልቅስ ልሰዎች ያለውን አላማ እና እቅዲ የሚያብራራ መጽሃፍ ነው። ስለዚህም እውነተኛ ስነ መለኮታዊ ትምህርት ትኩረቱን በ እግዚአብሄር አላማ እና በከርስቶስ ስለገለጠው ፈቃዱ የሚያተኩር ነው። በኃጥያተኛ ህሊና ተዘፍቆ የማይገደበውን፤የማይብራራውን ፤የማይለካውን የ እግዚአብሄር ማንነትና ክብር ለማስርዳት እንደመዋተት አክሳሪ ነገር ምን አለ? ይልቅስ ለማዋቅ መጣር ያለብን ለኃትያተኛው ልባችን ስለተገለጠው በረከት እና ጸጋ ነው።
ለዚህም ነው ሃዋርያው ጳውሎስ የእየሱስ ክርስቶስን መሰቀል ማስተማር ለ አይሁዶች መሰናከያ ነው ለ ግሪኮች ሞኝነት ነው እግዚአብሄር ግን ኃይሉንና ጥበቡን ኢየሱስ ውስጥ አስቀመጠ። ዛሬ የእግዚአብሄርን ጥበብ እምናገኘው የትሰቀለውን ኢየሱስ ክርስቶስን በጥልቀት በመመልከት ብቻ ነው። ከሰማይ ወረደ… አብሮን ኖረ… ተሰቃየ… ተሰቀለ… ሞተ በግልጽ በፊት ለፊታችን የቀረበ ለመረዳት የማያስቸግር ግልጽነት ነው። ስለዚህ ልባችንና አይናችን እርሱ ላይ ተቀርቅሮ ቢቀርስ? ግልጹን ኢየሱስን ካየን ስለዚህ ምን አይነት እግዚአብሄር ነው ያለው በማለት ሰማይ ላይ ለምንጠላጠል ከመሞከር እንተርፋለን።
ዛሬ ዛሬ ብዙ ጨቁኞች መካከለኛውን ኢየሱስ ክርስቶስን እራሱ በ እኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም ያለውን ጌታ አስወጥተውት ኑ እግዚአብሄርን እናሳያችሁ ይሉናል ያለ የእየሱስ ወደ እግዚአብሄር አብ የሚወስድ መንገድ የለም እኮ ። ነጻነታችንን በእስራት ህይወታችንን በዘላለም ሞት ሊቀዩርብን የሚዳክሩ በግብዝነታቸው የሚያታልሉን ጭፍን መምህራን ናቸው።
ስለ እግዚአብሄር ማንነት ከ ጽድቅ ትምህርት ውጪ ብንከራከር እጅግ ታዋቂ ልንሆን እንችላለን። ነገር ግን ስለ ህሊና ፤ ኃጥያት፤ህግ፤ሞት እና ሰይጣን ለማጥናት ስለ እግዚአብሄር ማንነት ያሉንን ጥያቄዎች በማቆም በኢየሱስ ላይ ማተኮር አለብን። ኢየሱስ እናንተ ሸክም የከበዳችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለው እንዳለው ማለት ነው። በ እየሱስ ውስጥ የጥበብ እና የ እውቀት ሁሉ መዝገብ አለ። የ እውነተኛ እግዚአብሄር አምሳል እርሱ እየሱስ ከርስቶስ ብቻ ነው። ለዛም ነው ጳውሎስ ጸጋና ሰላም ከ የሱስ ክርስቶስም ይሁን ያለው። በ እግዚአብሄር ማንነት ላይ ብቻ የሚደረግን ጉጉት ለማስጠንቀቅም ነው እየሱስን እንድሰማውም ነውሊያስተምረን የፈለገው።
አርዮስም ይሁን መሀመድ ስለ እየሱስ የተናገሩት አሳሳች ትምህርት ነው። እየሱስን ከ እግዚአብሄር የተፈጠረ አድርገው አቅርበዋል። ጳውሎስ ግን እየሱስ ጌታን ከግዚአብሄር እኩል የጸጋ እና ሰላም ምንጭ አድርጎ አቅርቧል። እግዚአብሄር ብቻ ሊሰጥ የሚቻለውን ጸጋ እና ሰላም ኢየሱስም እንደሰጠ በዚህም የ እየሱስን መለኮትነት አሳይቷል።
ክፉ ከሆነው ከ አሁኑ ዓለም ፡ ዓለምን ክፉ ያለበት ምክንያት ዓለም በአለመታዘዝ ፤ በግድየለሽነት ፤ በጥላቻ የተሞላች የሰይጣን አገዛዝ የሰፈነባት በመሆኗ ነው። ስለዚህ ማንም በገዛ ችሎታው ኃጥያቱን ማስወገድ እስካልቻለ ድረስ ለሰይጣን እና ግዛቱ አጎብዳጅ ነው። ለዛም ነው በክርስቶስ መንግስት ያልተጠቃለለ ሁሉ ባሉት እና ባዳበረው ችሎታዎቹ ሰይጣንን ማገልገሉ አይቀሬ ነው። ለምሳሌ እውቀትን እንውሰድ ያለ ክርስቶስ የሆነ እውቀት ሁሉ እየሱስ ክርስቶስን ሞኝነት አድርጎ ይሰብካል። ያለ ክርስቶስ የሆነ መልካምነት ሁለት እጥፍ ኃጥያት ነው። ምክንያቱም እነዚህ እውቀቶች እየሱስን አልቀበልም ማለታቸው ብቻ ሳይሆን ሰዎችንም እንዳይቀበሉ በመሸወድ ወደ ኋላ ያስቀራሉ ይህም በክርስቶስ የሆነውን የእግዚአብሄርን የድነት አካሄድ እንደማጣጣል ነው። ጳውሎስ ይህ ዓለም በጣም ምርጥ ሆንኩ ሲል በጣም የዘቀጠ ክፉ ሆነ ማለት ነው እያለን ነው። የዓለም ክፋት መለኪያ ሰዎች የክርስቶስን ጽድቅ መቀበል እንዳይችሉ ባደረገበት ልክ የሚለካ መሆን አለበት። “ ከ ክፉ ዓለም ያድነን” ዘንድ ሲለን ማንም ሌላ ከዚህ ዓለም ክፋት ሊያድነን እንደማይችል እየነገረን ነው። ጳውሎስ ይህ ዓለም ከነ እውቀቱ ፤ ሃይሉና እና ጽድቁ በክፉ እስር ስለሆነ ያድነናል ያለን ከዚህ ዓለም ንብረቶች ነው። ከሰይጣን እስራት ይፈታን እግዚአብሄር ምስጋና ይገባዋል። የእግዚአብሄር መንግስት በጸጋ፤ በጽድቅ፤ በዘላለማዊ ህይወት፤ በኃጥያት ስርየት፤ በሰላም ፤ በብርሃን የተሞላች ናት። እየሱስ ባረገ ጊዜ ለመቅደላዊት ማርያም ለወንድሞቼ ንገሪ ወደ ወደ አባቴ ና አባታችሁ ወደ አምላኬ ወደ አምላካችሁ እሄዳለው እንዳለ እግዚአብሄር አምላካችን እና አባታችን የሆነው በክርስቶስ እየሱስ ወንድማዊነት ነው።
ጳውሎስ እየሱስ ራሱን ሰጠ ይላል። የሰጠን ንብረት ወይም ወርቅ ሌላ የሚታዩ ነገሮች አይደሉም። በሰው እጅ የሚገባ ምድራዊ ነገር አልሰጠንም። ራሱን የሰጠን ደግሞ ለመልካምነታችን ወይም በጎ ምግባራችን ምላሽ አይደለም እያለን ነው። ለኃጥያታችን ነው ራሱን የሰጠን።
ሁሌም በታላቅ ፍርሃትና መንቀጥቀጥ ክብር የሚገባው እግዚአብሄር አምላካችን እንደሆነ ጳውሎስ በመጨረሻ ያሳያል። ወንድሞች ሁሌም እግዚአብሄርን በማክበር መሆን ከጥንት ሃዋርያት የነበረ መሆኑን እናይበታለን።
ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ለ እግዚአብሄር ይሁን!
Comments
Post a Comment